የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በ5ኛ ዙር ኮርስ ለአዲስ ለተመለመሉ ዕጩ የሰላም ሰራዊት አባላት የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና በጉለሌ ክፍለ ከተማ አስጀመረ ፡፡
ቢሮው ከጉለሌና ክፍለ ከተማ የተወጣጡ 1ሺህ አዲስ ምልምል ዕጩ የሰላም ሰራዊት አባላት የንድፈ ሃሳብና ወታደራዊ ስልጠና ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሄዷል።
በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃለፊ አቶ ሀብታሙ ደረጀ እንደተናገሩት የሰላም ሰራዊት አባላት የከተማችንን ሰላምና ጸጥታ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን ሀገራዊና ከተማዊና ሃይማኖታዊ የአደባባይ ክንውኖች በሰላም እንዲከናወኑ ትልቅ ድርሻ ተወጥታችኋል ያሉ ሲሆን አዲስ ምልምል የሰላም ሰራዊት አባላት ያገኛችሁትን ስልጠና በተግባር በማዋል የድርሻችሁን ማበርከት ይገባችኋል ብለዋል፡፡
የሰላም ሰራዊቱ የሰላም አምባሰደርነቱን በተግባር እያረጋገጠ ከውስጥ ከውጪ የሚነሱ ግጭቶችን በመመከት በዛሬው ዕለት ከጉለሌ የገባችሁ አንድ ሺህ አዲስ ምልምል የሰላም ሰራዊት አባላት የአካባቢያችሁን እንዲሁም ክፍለ ከተማችሁን ሰላም ጸጥታ ከጸረ ሰላም ሃይሎች በመጠበቅ የተሰጣችሁን ኃላፊነት በተግባር መወጣት አለባችሁ ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ምክትል ቁጥጥርና እርምጃ አወሳሰድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከፍያለው ታደሰ በበኩላቸው የሰላም ሰራዊቱ ለከተማችን ሰላም ዘብ በመቆም ላደረጋችሁት አስተዋጽዖ አስተዳደሩ ትልቅ ክብር አለው ያሉ ሲሆን በከተማችን ከ11ዱም በክፍለ ከተማ የተወጣጡ 11ሺህ የሰላም ሰራዊት የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና ይወስዳሉ ብለዋል ፡፡